1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የህወሓት አባላት ናቸዉ የተባሉ ታጣቂዎች ተማሪዎችን አፈኑ፣ ቤት አቃጠሉም

ኢሳያስ ገላው
ረቡዕ፣ ግንቦት 5 2018

በራያ አላማጣ ከተማ በሚገኘው የኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን ጉባኤ ቤት ይማሩ የነበሩ ከ50 በላይ የአብነት ተማሪዎች በከተማው ውስጥ በሚንቀሳቀሱ የህወሃት ታጣቂዎች ታፍነው መወሰዳቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እና የአብነት ተማሪዎች ገለጹ።

https://p.dw.com/p/5DiP9
ተማሪዎቹን ያገቱት የህወሓት ታጣቂዎች መሆናቸዉን ከእግታዉ ያመለጡ ተማሪዎችና ነዋሪዎች አስታዉቀዋል
የአላማጣ መሐል ከተማ።በከተማይቱ ዉስጥ የነበሩ ሐምሳ የቤተ,-ክሕነት ተማሪዎች በታጣቂዎች ታግተዋልምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

የህወሓት አባላት ናቸዉ የተባሉ ታጣቂዎች ተማሪዎችን አፈኑ፣ ቤት አቃጠሉም

በራያ አላማጣ ከተማ በሚገኘው የኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን ጉባኤ ቤት ይማሩ የነበሩ ከ50 በላይ የአብነት ተማሪዎች በከተማው ውስጥ በሚንቀሳቀሱ የህወሃት ታጣቂዎች ታፍነው መወሰዳቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እና የአብነት ተማሪዎች ገለጹ። በተማሪዎቹ ላይ ከፍተኛ ድብደባ መፈጸሙን የሚናገሩ አስተያየት ሰጪዎችም በድርጊቱ በርካታ ታጣቂዎች መሳተፋቸውን ይናገራሉ።

« ጉባይ  ጨርሰው ወደ ቤታቸው ከሄዱ በኋላ ገብተው ተማሪውን በሙሉ በዱላ መቱት። ወዲያው ወታደሮቹ ደግሞ ሁሉም መጡ ከወታደሮቹ። ግማሻችን ዝም ብለን ሸሸን። 'እንረሽናቸው! እንረሽናቸው!' እያሉ አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ አንዳንዶች በቃ 'እንረሽናቸው' ሲሉ እዛ እንደምንም ብለው ለቀቁን። ምንም ነገር ሲያጡብን ወታደሮቹ በቃ ወታደሮች ናቸው በቃ። የህወሃት ናቸው ሌላ ምንም የለም ተጨማሪ የለም። እነሱ ናቸው በቃ።"

700 የሚደርሱ ተማሪዎች የሚማሩበት ጉባኤ ቤት እና የተማሪዎች መኖሪያ ጎጆ ሙሉ በሙሉ መቃጠላቸውን የሚናገሩት የአብነት ተማሪዎቹ ሁኔታው ለህይወታቸው አስጊ በመሆኑም አካባቢውን ለቅቀው መሰደዳቸውን ይገልጻሉ።"በበነገታዉ ጉባኤውን አቃጠሉብን። ጉባኤ ቤቱ ተቃጥሎ ሙሉ በሙሉ የተወሰነ ብቻ ነው የሚተርፈው አቃጥለውታል። 700 ተማሪ ነው የሚኖርበት። ህዝቡ ነው ሌሊት ግማሹን ያተረፈው። እኛ ዉጡ ተብለን ሊገድሉን ሲሉ ከዛ ወጥተን እኛ ዝም ብለን ሄደን በየአረጋዊዉ ቤት በየሶስት በሁሉ ተበተንን በጫካ ውስጥም ብለን አደርን። ከዛ ወዲያ አቃጠሉት ለምርጫ ነዉ ወይ የሸከፉችሁ  ይሄ ሁሉ ተማሪ ምንድነው እያሉ እንትን አሉ።"

 

 ከታሰሩት የአብነት ተማሪዎች መካከል ነበርኩ የሚለው አስተያየት ሰጪም ከአድካሚ የጉልበት ስራ በኋላ እሱ መፈታቱን ገልጾ ሌሎች ግን የት እንደደረሱ እንደማያውቅ ይናገራል።"እኔ አብሬያቸው ከተያዙት ከስረኞቹ   አንዱ ነኝ። አብረን ነው የሄድነው። ወደ ሰማኒያ ዙሮ ይደርሳል። ከዚያ ደግሞ እናሰልጥናችሁ ብለው ደግሞ ሌላ ሁሉ ይዘው ሄደዋል። ግን በቃ አይታወቅም በቃ ተማሪውን እንዴትና የት እንዳደረሱት። ግማሹን በሌላ  ወስደዋል። በሌላ ገብተው ወስደዋል። ዞሮ ዞሮ ያልተገኘ ብዙ ተማሪ አለ። ማነው ዝም ብሎ ተማሪው ሌሎች ስልክ ብንደዉልም ስልካቸዉ የማይሰራ  የት እንደሄዱ የማይታወቅ ተማሪ አለ ።"

የህወሓት አባላት ናቸዉ የተባሉ ታዛቂዎች ከአለማጣ ከተማ 50 የቤተ-ክሕነት ተማሪዎችን አግተዋል
የራያ አለማጣ ከተማ በከፊልምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ሞገስ ሃይሉ በአላማጣ ከተማ የኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን በግለሰቦች መካከል በተነሳ ግጭት የጉባኤ ቤቱ በእሳት ተቃጥሎ መውደሙንና ድርጊቱን የፈጸመውን ሰው ይዘው የማጣራት ስራ በመስራት ላይ መሆናቸውን ይገልጻሉ።"የተፈጠረው የግለሰቦች ችግር ነው። የቆሎ ተማሪዎች አሉ እዛው ጋ። ከዚያ አካባቢ ከሚኖሩ ግለሰቦች ጋር ግጭት ፈጠሩ። ከዚያ ተደባደቡ። ከተደባደቡ በኋላ በአጋጣሚ እነዛ ቆሎ ተማሪዎች ከማህበረሰቡ አካል የሆነ ልጅ በዱላ ደብድበውት ነበረ። በጣም ስለተመታ ብሶቱን ለመግለጽ ሄዶ የዛ የተጣላው ልጅ ጎጆ ነበረች። ያው ሲያቃጥላት እሷን እንዳለ ክርቢት ሙሉ በሙሉ ተቃጠለ። ስለዚህ እንደዛ ያደረገው ተጠርጣሪ አካል በህግ ስር ውሏል።"

በእለቱ በጥርጣሬ የአብነት ተማሪዎችን አስረን ነበር የሚሉት ከንቲባ ሞገስ በጥርጣሬ የያዝናቸውን ለቀን በግጭቱ ውስጥ ተሳትፈዋል ያልናቸውን ግን አሁንም በቁጥጥር ስር እንዲቆዩ አድርገናል ይላሉ።"ከተማውን እኔም አስተዳድራለሁ። መጀመሪያ በመጠርጠር ዝም ብለን ብዙ አስረን ነበረ፣ ምንም የሚዋሽ ነገር የለም። ከዚያ በኋላ ግን ካጣራን በኋላ እነሱን ለቀን የተጣሉትን አካላት ብቻ ለይተን ይዘን አሁን እነሱን ብቻ ነው እያጣራን ያለነው። ሌላውን ግን ፈትተን ልከናለል።"

ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ መልኩ አራት የጉባኤ ቤቱ ተማሪዎች በስለት ተወግተው እንደነበረም ተገልጿል። 

ኢሳያስ ገላዉ

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር