የሙሴቪኒ 40ኛ ዓመት የስልጣን ዘመን እና የዩጋንዳ ፈተናዎች
ቅዳሜ፣ ግንቦት 8 2018
የዩጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ባለፈው ማክሰኞ ሰባተኛ ተከታታይ የስልጣን ዘመናቸውን የሚያስጀምራቸውን ቃለ መሃላ ፈጽመዋል። የበርካታ ምስራቅ አፍሪቃዉኢን የፖለቲካ መሪዎች በጦር ከታመሰች ሀገር በወታደራዊ መለዮ የተገለጡት ሰው እንደምን አራት አስርት ዓመታትን በስልጣን ላይ ቆዩ ፤ ዩጋንዳንስ ከየት አንስተው የት አደረሱ ሲሉ ይጠይቃሉ ።
ካምፕላ በደመቀ ስነስረዓት ያከበረችላቸው የፕሬዚዳንቱ በዓለ ሲመት የርሳቸውን ቀጣናዊ የዲፕሎማሲ ተሰሚነት ያሳየ እንደነበር ከፍ ብሎ ተደምጧል። የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ፊሊክስ ቲሺሴኬዲ፣ የታንዛኒያዋ ሳሚያ ስሉሁ ሀሰን፣ የናይጄሪያው ቦላ ቲኑቡ እና የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታን ጨምሮ በርካታ ቀጣናዊ መሪዎች ወደ ዩጋንዳ መዲና ካምፓላ ከተጓዙ የሀገር መሪዎች እና የቀጣናው ተጽዕኖ ፈጣሪ ፖለቲከኞች ተጠቃሾች ናቸው።
ሙሴቪኒ በጥር ወር በተካሄደውና የተቃዋሚዎች መታሰር እና ማስፈራራት በነበረበት ድባብ 72 በመቶ ያህል ድምፅ በማግኘት ቢያሸንፉም፣ ብዙዎች የ81 ዓመቱ መሪ ወደ ስልጣን ዘመናቸው ማክተሚያ እየተቃረቡ መሆኑን ያምናሉ። ይሁን እንጂ ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው ዩጋንዳውያን ገና ብዙ የሚሰሩ ስራዎች ገና እንዳሉ ይናገራሉ። የካምፓላ ነዋሪው አዶልፍ ምባይኔ
"በአጠቃላይ አሁን በዩጋንዳ ሰላም አለ። ሰላም ሲኖር ደግሞ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች የማደግና የመስፋፋት ዝንባሌ አላቸው"
የኢኮኖሚ እድገት እና የወጣቱ ትውልድ እጣ ፈንታ
አብዛኞቹ ዩጋንዳውያን በሙሴቪኒ አገዛዝ ስር ዩጋንዳ ከፍተኛ የፖለቲካ መረጋጋት እና የኢኮኖሚ እድገት እንዳስመዘገበች ይስማማሉ። እንደ ዓለም ባንክ መረጃ፣ የዩጋንዳ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት እድገት በጎርጎርሳዉያኑ 2024 ከ6% በላይ የነበረ ሲሆን፣ በ1986 ከነበረበት 3.9 ቢሊዮን ዶላር በ2024 ወደ 53.9 ቢሊዮን ዶላር አድጓል።
ነገር ግን የህዝብ ቁጥሩም በዚያው ልክ ማደጉ ነው የሚነገረው። በተጠቀሰው ዓመት ዩጋንዳ ከነበራት ከ15.5 ሚሊዮን የህዝብ ቁጥር ወደ 50 ሚሊዮን አድጓል። አሃዙ እንደሚያሳየው አማካይ ዕድሜው 17 ዓመት የሆነ የዓለማችንን ትንሹን ወጣት ህዝብ የፈጠረ ቢሆንም፣ ስራ አጥነት ግን የሀገሪቱ ዋነኛ ስጋት መሆኑ ነው የሚነሳው። ጋዜጠኛ ሮበርት ኪራቦ በካምፓላ ያለውን ሁኔታሲገልጽ እንዲህ ይላል።
"በጣም ግዙፍ የህዝብ ቁጥር አለን። አብዛኛው ወጣት ነው፣ ከነዚህም ውስጥ በርካቶቹ ስራ አጥ ናቸው። ይህ ደግሞ የሚፈነዳ ቦምብ ነው"
የኢኮኖሚ ባለሞያዋ እና የቀድሞ የፓርላማ አባልዋ አግነስ አቲም አፔያ በበኩላቸው ህዝቡ በተግባር የሚታይ ለውጥ እንደሚፈልግ ይናገራሉ።
"ዩጋንዳውያን ተጠያቂነትን ማየት ይፈልጋሉ። ኢኮኖሚው እያደገ መሆኑን እየሰሙ ነው፣ ነገር ግን ህዝባችን አሁን ያንን እድገት በተግባር ሊሰማው ይፈልጋል"
ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ባደረጉት ንግግር የሀብት ፈጠራን፣ የፀረ-ሙስና ጥረቶችን እና መሰረተ ልማትን እንደሚያሻሽሉ ቃል በመግባት የምስራቅ አፍሪካውያን እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል፦
ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ድምጽ
"ዩጋንዳዊያን ቤተሰቦች ሁሉ በአራቱ ዘርፎች ወደ ገንዘብ ኢኮኖሚ እንዲቀላቀሉ እና እዚህ ከእህት የአፍሪካ ሀገራት የመጡት ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞቻችን ሁሉ ጋር ስራ የሚያገኙበት በርካታ እድል ይፈጠራል"
ይህ የፕሬዚዳንቱ ንግግር በርግጥ በካምፓላ ጎዳናዎች ላይ የተለያየ ስሜት ፈጥሯል። ዴቪድ ሴኪምፒ የተባሉ ፓስተር "በፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ ላይ ትልቅ እምነት አለን፣ ያለንን ህልምም ያሳካልናል" ሲሉ እምነታቸውን ጥለውባቸዋል። የጎዳና ላይ ተንቀሳቃሽ ነጋዴው ጁስተስ ኪዛ ግን "ባለፈው የስልጣን ዘመን ፕሬዝዳንቱ የነጋዴዎችንና የጎዳና ላይ ሻጮችን ጉዳይ በአግባቡ አልያዙትም " በማለት ቅሬታውን ገልጿል። የማኬሬሬ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዋ ጆቭሌት ሳራ ናንኪንጋ ደግሞ የህዝብ ገንዘብ ምዝበራ ችግር መሆኑን ጠቅሳ፣ መንግስት "ለወጣቶችና ለስራ ፈጣሪዎች የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ማሻሻል" እንዳለበት ተናግራለች።
የፖለቲካው ድባብ መከርረር
በሌላ በኩል፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች በዩጋንዳ ያለው የሲቪክ ምህዳር እየጠበበ እና የፖለቲካ ጭቆና እየጨመረ መምጣቱን ያስጠነቅቃሉ። የተቃዋሚ መሪው ቦቢ ዋይን በምርጫው ወቅት የደረሰባቸውን እንግልት እና መሰደድ እንደ ማሳያ ያነሳሉ ። አንጋፋው ፖለቲከኛ ኪዛ ቤሲግዬም በእስር ላይ ናቸው።
ምሁሩ አዶልፍ ምባይኔ ይህንን ሲያብራሩ እንዲህ ይላሉ
"ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ ሰዎች የመንግስትን እንቅስቃሴዎችና ፕሮግራሞች በግልጽ የሚተቹበት ምህዳር እየጠበበ፣ ለተቃራኒ አመለካከቶች ያለው መቻቻልም እየቀነሰ የመጣ ይመስለኛል" ብለዋል።
አሁን ጥያቄው ፕሬዚዳንቱ የሆነ ጊዜ ላይ ማን ሊተካቸው ይችላል የሚለውም ጎልቶ ይሰማል።
የሙሴቪኒ ተተኪ ማን ይሆናል?
የሙሴቪኒ የስልጣን ዘመን እስከ 2031 የሚቆይ ቢሆንም፣ እስካሁን በይፋ ተተኪ አልሰየሙም። ይህ ደግሞ ሌላው ትልቅ ስጋት መሆኑን አዶልፍ ምባይኔ ይናገራሉ፦
"ይህ ለብዙዎቻችን ትልቅ ስጋት ነው፤ ምክንያቱም በሂደት ለሰላማዊ እና ስልታዊየፖለቲካ ስልጣን ሽግግር የሚሆን የተደራጀ ዝግጅት ይኖራል ብለን አስበን ነበር"
የሙሴቪኒ ልጅ ጀነራል ሙሆዚ ካይኔሩጋባ እንደ እጩ ተፎካካሪ ቢታዩም፣ የርሳቸው የፊት ለፊት ግጭት ባህሪ ከሙሴቪኒ የማራኪ የፖለቲካ ባህሪ ጋር እንደሚቃረን ነው የሚነገረው።
አግነስ አቲም አፔያ ግን ሀገሪቱ ከግለሰቦች አምልኮ መውጣት አለባት ብለው ያምናሉ፦
አግነስ አቲም አፔያ፦ድምጽ
"እንደ ሀገር ዩጋንዳን እንደ ሙሴቪኒ የግል ንብረት አድርጎ ከመመልከት መራቅ መጀመር አለብን ብዬ አስባለሁ። ከግለሰቦች መራቅ አለብን፣ ምክንያቱም መልካም አስተዳደር ሁልጊዜ የሚለካው በስርዓቶች፣ በብቃት እና በቀጣይነት ነው"
የቀድሞውን የኢዲ አሚን እና የሚልተን ኦቦቴን ዘመን ሁከት ያሳለፉት ሄንሪ ባጉማ ሙሴቪኒ "ለነገ የተሻለ ታሪክ ለማስቀመጥ የተቻለውን ሁሉ አድርጓል... እኛ ግን ተርፈናል" ቢሉም፣ አዶልፍ ምባይኔ ግን ለወደፊቱ የሚከተለውን ጠንካራ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ይደመድማሉ፦
የዩጋንዳ የረጅም ጊዜ መሪ ዩዌሪ ሙሴቪኒ 40ኛ ዓመት የስልጣን ዘመናቸውን ሲጀምሩ፣ ሀገሪቱ በኢኮኖሚ እድገት፣ በወጣቶች ስራ አጥነት እና በስልጣን ሽግግር ስጋቶች መካከል መያዟ ግን ለዩጋንዳዉያን የማንቂያ ደውል ይሆንላቸው ይሆን ?
ካይ ኔቤ/ ታምራት ዲንሳ