የብሪክስ ስብሰባ፤ የኢራን ጦርነት ቀዉስና የነዳጅ ዋጋ ንረት ጉዳይ ሸብቦታል
ሐሙስ፣ ግንቦት 6 2018
ሕንድ መዲና ኒዉ ደልሒ ዉስጥ ዛሬ የተሰበሰቡት የ BRICS አባል ሐገራት የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች፣ ዩናይትድ ስቴትስና እስራኤል በኢራን ላይ በከፈቱት ጦርነትና መዘዙ ላይ እየተነጋገሩ ነዉ። BRICS በሚል ምሕጻረ ቃል የሚጠራዉ ስብስብ ዋና ዓላማ ምጣኔ ሐብታዊ ቢሆንም እንደ አብዛኞቹ ተመሳሳይ ማህበራት ፖለቲካዊ ጉዳዮች እየተጫኑት ሆንዋል።
ለሁለት ቀናት የሚመክረዉን ሥብሰባ የሚያስተናግዱት የሕንድ የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሱብራሕማንያም ጃይሳንከር ለተሰብሳቢዎች እንደነገሩት ምዕራብ እስያ ላይ የተጫረዉ ግጭት «ልዩ ትኩረት ይሻዋል።» የሕንዱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አክለዉም የሆርሙዝ ወሽመጥን ጨምሮ በዓለም አቀፍ የባሕር መስመመሮች ላይ የሚደረግ ዝዉዉር «ለዓለም ምጣኔ ሐብት ወሳኝ ነዉ» ብለዋል። የኢራን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አባስ አራግቺ በበኩላቸዉ «ዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰዋል» ያሏቸዉን ዩናይትድ ስቴትስና እስራኤልን የBRICS አባል ሐገራት እንዲያወግዙ ጠይቀዋል። አራግቺ እንደሚሉት ዩናይትድ ስቴትስና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱትን ጦርነት «ሕገ ወጥ፣ የተስፋፊነትና የጦርነት ናፋቂዎች ምግባር» በማለት አዉግዘዉታል።
ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድና ቻይና የመሠረቱት BRICS፣ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ 2011 ደቡብ አፍሪቃን፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲሕ ደግሞ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ኢንዶኔዥያን፣ ኢራን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን በአባልነት ያስተናብራል። ግብፅና ኢትዮጵያ በአባይ ዉኃ አጠቃቀም ሰበብ ይወዛገባሉ። ኢራንና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በኢራን ላይ በተከፈተዉ ጦርነት ምክንያት ዓይንና ናጫ ናቸዉ።
አዜብ ታደሰ / ነጋሽ መሐመድ
ዮሃንስ ገብረግዚአብሔር